ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 15:18-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በተናገርሁትና በአደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤

19. ይህም የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ።

20. ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር።

21. ይልቁንም፣“ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

22. በዚህም ምክንያት ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ።

23. አሁን ግን በእነዚህ አካባቢዎች የምሠራው ስለሌለ፣ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ እናንተን ለማየት እናፍቅም ስለ ነበር፣

24. ይህን ዕቅድ ወደ እስጳንያ በምሄድበት ጊዜ ልፈጽመው አስባለሁ። በማልፍበትም ጊዜ ልጐበኛችሁና ከእናንተ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ በጒዞዬ እንደም ትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

25. አሁን ግን በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ነኝ።

26. ምክንያቱም መቄዶንያና አካይያ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል የሚገኙትን ድኾች ለመርዳት ተነሣሥተዋልና።

27. ርዳታ ለማድረግ ወደዋል፤ በርግጥም ባለ ዕዳዎቻቸው ናቸው። አሕዛብ የአይሁድ መንፈሳዊ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ፣ ያገኙትን ምድራዊ በረከት ከአይሁድ ጋር ይካፈሉ ዘንድ የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው።

28. ስለዚህ ሥራውን ከጨረስሁና ይህን ፍሬ መቀበላቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ እግረ መንገዴንም እናንተን አያለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 15