ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 9:29-43 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ከግሪክ አገር ከመጡት አይሁድ ጋር እየተነጋገረ፣ ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ጥረት ያደርጉ ነበር።

30. ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ፣ ወደ ቂሳርያ አውርደው ወደ ጠርሴስ ሰደዱት።

31. በዚህ ጊዜ በይሁዳ፣ በገሊላና በሰማርያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር ጀመረች፤ ተጠናከረችም። ደግሞም እግዚአብሔርን በመፍራት እየተመላለሰችና በመንፈስ ቅዱስ እየተጽናናች በቍጥር እየበዛች ሄደች።

32. ጴጥሮስም ከአገር ወደ አገር በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ በልዳ የሚኖሩትን ቅዱሳን ለመጐብኘት ወረደ።

33. በዚያም ኤንያ የተባለ፣ ስምንት ዓመት የዐልጋ ቍራኛ የነበረ አንድ ሽባ ሰው አገኘ።

34. ጴጥሮስም፣ “ኤንያ ሆይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣና መኝታህን አንጥፍ” አለው። ኤንያም ወዲያውኑ ብድግ አለ።

35. በልዳና በሰሮና የሚኖሩትም ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ተመለሱ።

36. በኢዮጴ ጣቢታ የተባለች አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፤ የስሟም ትርጓሜ ዶርቃ ማለት ነው። እርሷም ዘወትር በትጋት በጎ ነገር እያደረገችና ድኾችን እየረዳች ትኖር ነበር።

37. በዚያ ጊዜም ታማ ሞተች፤ ሰዎችም አስከሬኗን አጥበው በሰገነት ላይ ባለው ክፍል አስቀመጡት።

38. ልዳ ለኢዮጴ ቅርብ ስለ ነበረች፣ ደቀ መዛሙርትም ጴጥሮስ በልዳ መሆኑን በሰሙ ጊዜ፣ ሁለት ሰዎች ልከው፣ “እባክህ ፈጥነህ ወደ እኛ ና” ሲሉ ለመኑት።

39. ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ እዚያ በደረሰ ጊዜም ሰገነት ላይ ወዳለው ክፍል አወጡት። መበለቶቹም ሁሉ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር በነበረችበት ጊዜ ያደረገቻቸውን ቀሚሶችና ልብሶች እያሳዩት ዙሪያውን ከበው ያለቅሱ ነበር።

40. ጴጥሮስም ሁሉንም ከክፍሉ አስወጥቶ ተንበርክኮ ጸለየ፤ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ፣ “ጣቢታ፤ ተነሺ” አለ። እርሷም ዐይኗን ገለጠች፤ ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ቀና ብላ ተቀመጠች፤

41. እርሱም እጇን ይዞ አስነሣት፤ አማኞችንና መበለቶቹንም ጠርቶ ከነሕይወቷ አስረከባቸው።

42. ይህም ነገር በመላው ኢዮጴ ታወቀ፤ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ።

43. ጴጥሮስም ስምዖን ከተባለ ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋር በኢዮጴ ብዙ ቀን ተቀመጠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 9