ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 28:14-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን አብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን።

15. በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ፣ እንዲሁም ‘ሦስት ማደሪያ’ እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም።

16. ሮም በደረስን ጊዜም፣ ጳውሎስ ይጠብቀው ከነበረው ወታደር ጋር፣ ለብቻው በዚያ እንዲቈይ ተፈቀደለት።

17. ከሦስት ቀንም በኋላ፣ ጳውሎስ የአይሁድን መሪዎች በአንድነት ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ፣ ሕዝባችንን ወይም የአባቶቻችንን ሥርዐት የሚቃረን ምንም ሳላደርግ፣ በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል።

18. እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስላላገኙብኝ፣ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር፤

19. አይሁድ በተቃወሙ ጊዜ ግን፣ ለቄሳር ይግባኝ ማለት ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ምክንያት ኖሮኝ አይደለም።

20. እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር የጠራኋችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።”

21. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም።

22. ይሁን እንጂ፣ ሰዎች ስለዚህ የእምነት ክፍል በየቦታው ክፉ እንደሚያወሩበት እናውቃለን፤ የአንተ አስተያየት ደግሞ ምን እንደሆነ መስማት እንፈልጋለን።”

23. ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ፣ ብዙ ሆነው ወደ ማረፊያ ስፍራው መጡ፤ እርሱም ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ሞከረ።

24. አንዳንዶቹ እርሱ የሚለውን አምነው ተቀበሉ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑበትም፤

25. እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም፤ ጳውሎስም እንዲህ የሚል የመጨረሻ ቃል ከተናገራቸው በኋላ ሄዱ፤ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል እንዲህ ብሎ ተናግሮአል፤

26. “ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ እንዲህም በላቸው፤“መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ማየትን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትመለከቱም።”

27. የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና፤ጆሮአቸውም ተደፍኖአል፤ዐይናቸውንም ጨፍነዋል።አለዚያማ፣ በዐይናቸው አይተው፣በጆሮአቸው ሰምተው፣በልባቸው አስተውለው፣ይመለሱና እፈውሳቸዋለሁ።’

28. “ስለዚህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።”

29. ይህንንም ከተናገረ በኋላ፣ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።

30. ጳውሎስም ራሱ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደስታ ይቀበል ነበር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 28