ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ጴጥሮስ 2:2-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ብዙዎች አስነዋሪ ድር ጊቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።

3. እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዙዋችኋል። ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፊያቸውም አያንቀላፋም።

4. እግዚአብሔር ኀጢአት የሠሩትን መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ከጣላቸውና በጨለማ ጒድጓድ ውስጥ ለፍርድ ካስቀመጣቸው፣

5. የጽድቅ ሰባኪ የነበረውንም ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣

6. ደግሞም ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው፣

7. ጻድቅ የሆነውንና በዐመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት እየተሣቀቀ የኖረውን ሎጥን ካዳነ፣

8. ያ ጻድቅ ሰው በእነርሱ መካከል ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው ነገር ነፍሱ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ድርጊታቸው ብትጨነቅም፣

9. ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።

10. በተለይም በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል።እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለሆኑ ሰማያውያንን ፍጡራን ሲሳደቡ አይፈሩም፤

11. ነገር ግን መላእክት ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ኀያል ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም።

12. እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በስሜታቸው ብቻ እንደሚመሩና ልቦናም እንደሌላቸው አራዊት ናቸው፤ የሚጠፉትም እንደ እንስሳት ነው።

13. ለዐመፃቸው የሚገባውን የዐመፅ ዋጋ ይቀበላሉ፤ በጠራራ ፀሓይ ሲፈነጥዙ እንደ ደስታ ይቈጥሩታል፤ በግብዣ ላይ ሳሉ ነውረኞችና ርኩሶች ሆነው ከእናንተም ጋር በፍቅር ግብዣ ላይ ይቀመጣሉ፤

14. ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ስስትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው!

15. ቀናውን መንገድ ትተው፣ የዐመፅን ደመወዝ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤

16. እርሱ ግን ስለ መተላለፉ ተገሥጾአል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት ገታ።

17. እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤

18. ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ጴጥሮስ 2