ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 17:6-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ።

7. በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ (ኤሎሂም) እሆናለሁ።

8. ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣለሁ፤ አምላካቸውም (ኤሎሂም) እሆናለሁ።”

9. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ።

10. አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ።

11. ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል።

12. የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ።

13. በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል።

14. የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።”

15. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን።

16. እኔ እባርካታለሁ ከእርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።”

17. አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ።

18. አብርሃም እግዚአብሔርን (ኤሎሂም)፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው።

19. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) እንዲህ አለ፤ “ይሁን እሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከእርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከእርሱ ጋር እገባለሁ።

20. ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ።

21. ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይስሐቅ ጋር አደርጋለሁ።”

22. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአብርሃም ጋር መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ።

23. በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር (ያህዌ) ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ገረዛቸው።

24. አብርሃም ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 17