ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፀአት 26:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “በቀጭኑ ከተፈተለ የበፍታ ድርና በሰማያዊ፣ በሐምራዊና በቀይ ማግ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች ማደሪያ ድንኳኑን ሥራ፤ እጀ ብልኅ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍባቸው።

2. መጋረጃዎች ሁሉ እኵል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሃያ ስምንት ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

3. አምስቱን መጋረጃዎች አገጣጥመህ ስፋ፤ የቀሩትንም አምስት መጋረጃዎች እንደዚሁ አገጣጥመህ ስፋቸው።

4. ከዳር በኩል ባለው መጋረጃ ጠርዝ ላይ፣ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶች አድርግ፤ በሌላውም የመጋረጃ ጠርዝ ላይ እንዲሁ አድርግ።

5. ቀለበቶችን ትይዩ በማድረግ አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው ጠርዝ መጋረጃ፣ አምሳ ቀለበቶችንም በሌላው ጠርዝ መጋረጃ አድርግ።

6. ከዚያም የመገናኛው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድ መጋረጃዎቹን በአንድ ላይ ለማያያዝ አምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሥራ።

7. “ማደሪያ ድንኳኑን ከላይ ሆነው የሚሸፍኑ ዐሥራ አንድ የፍየል ጠጒር መጋረጃዎች ሥራ።

8. ዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች እኩል ይሁኑ፤ የእያንዳንዱ ርዝመት ሠላሳ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን።

9. አምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ፣ እንደዚሁም ስድስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ አድርገህ ስፋቸው፤ ከማደሪያው ድንኳን ፊት ለፊት ስድስተኛውን መጋረጃ እጠፍና በላዩ ላይ ደርበው።

10. በአንድ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን፣ እንዲሁም በሌላ በኩል ባለው መጨረሻ መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶችን አድርግ።

11. ከዚያም አምሳ የናስ ማያያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝ በቀለበቶቹ ውስጥ ጨምራቸው።

12. ስለ ድንኳኑ መጋረጃዎች ትርፍ ቁመትም፣ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ ከማደሪያው ድንኳን ጀርባ ላይ እንዲንጠለጠል ይሁን።

13. የድንኳኑ መጋረጃዎች በሁለቱም ጐኖች አንድ ክንድ ርዝመት ይኖራቸዋል፤ የተረፈውም የማደሪያውን ድንኳን ጎኖች እንዲሸፍን ሆኖ ይንጠለጠላል፤

14. ለድንኳኑ በቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ ልብስ አብጅ፤ በላዩም ላይ የአቆስጣ ቆዳ ይሁን።

15. “ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አብጅ።

16. እያንዳንዱም ወጋግራ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወርዱም አንድ ክንድ ተኵል ይሁን፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፀአት 26