ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 6:7-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

9. “አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድ ይደር።

10. ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ።

11. ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ።

12. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምንጊዜም አይጥፋ። ካህኑ ጧት ጧት እሳቱ ላይ ማገዶ ይጨምር፤ በእሳቱ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያዘጋጅ፤ በዚህም ላይ የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ ያቃጥል።

13. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምንጊዜም አይጥፋ።

14. “ ‘የእህል ቊርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቊርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርቡት።

15. ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቊርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

16. የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ እርሾ ሳይገባበት በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት።

17. ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቊርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው።

18. ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለእርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”

19. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘሌዋውያን 6