ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16
  17. 17
  18. 18
  19. 19
  20. 20
  21. 21
  22. 22
  23. 23
  24. 24
  25. 25
  26. 26
  27. 27

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘሌዋውያን 6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

2. “ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በመካድና ባልንጀራውን በማጭበርበር ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔርንም (ያህዌ) ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣

3. ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማናቸውንም ኀጢአት ቢሠራ፣

4. በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤

5. በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ አምስተኛ በመጨመር ለባለ ንብረቱ ይመልስ።

6. ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤

7. በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።

የሚቃጠል መሥዋዕት

8. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

9. “አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድ ይደር።

10. ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ።

11. ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ።

12. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምንጊዜም አይጥፋ። ካህኑ ጧት ጧት እሳቱ ላይ ማገዶ ይጨምር፤ በእሳቱ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያዘጋጅ፤ በዚህም ላይ የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ ያቃጥል።

13. በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምንጊዜም አይጥፋ።

የእህል ቊርባን

14. “ ‘የእህል ቊርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቊርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርቡት።

15. ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቊርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

16. የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ እርሾ ሳይገባበት በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት።

17. ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቊርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው።

18. ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለእርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”

19. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

20. “አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርቡት ቊርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቊርባን አድርገው ያቅርቡት።

21. በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቊርባን ቈራርሰህ ሽታው እግዚአብሔርን (ያህዌ) ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ።

22. በእርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል።

23. ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቊርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”

የኀጢአት መሥዋዕት

24. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤

25. “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱም መሥዋዕት እዚያው በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይታረድ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

26. መሥዋዕቱንም የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ ይህም በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ በአደባባዩ ላይ ይበላ።

27. ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ ደሙ በልብስ ላይ ቢረጭ፣ ያንልብስ በተቀደሰ ስፍራ እጠብ።

28. ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ የናስ ዕቃ ከሆነ ግን ተፈግፍጎ በውሃ ይታጠብ።

29. ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

30. ነገር ግን ደሙ ለማስተስረያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ ቅድስት የቀረበው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ በእሳት ይቃጠል እንጂ አይበላ።