ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 7:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከእነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት፣ ዕዝራ የሠራያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ

2. የሰሎም ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የአኪጦብ ልጅ፣

3. የአማርያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣

4. የዘራእያ ልጅ፣ የኦዚ ልጅ፣ የቡቂ ልጅ፣

5. የአቢሱ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ፣ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፣

6. ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ። እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ የሕግ መምህር ነበር። የአምላኩ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ የጠየቀውን ሁሉ ንጉሡ ፈቀደለት።

7. እንደዚሁም አንዳንድ እስራኤላውያን፣ ከካህናት፣ ከሌዋውያን፣ ከመዘምራን፣ ከበር ጠባቂዎችና ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ጋር በመሆን በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሰባተኛው ዓመት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

8. ዕዝራ በንጉሡ ሰባተኛ ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ።

9. መልካሚቱ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ።

10. ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በማድረግ፣ ለእስራኤልም ሥርዐቱንና ሕጉን በማስተማር ራሱን ፈጽሞ ሰጥቶ ነበር።

11. እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን ሕግና ትእዛዝ ዐዋቂ ለነበረው ለካህኑና ለመምህሩ ዕዝራ ንጉሥ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

12. ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፤ ለሰማይ አምላክ ሕግ መምህር ለሆነው ለካህኑ ለዕዝራ፤ሰላም ለአንተ ይሁን፤

13. ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖርና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚፈልግ ማንኛውም እስራኤላዊ መሄድ እንዲችል ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

14. በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል።

15. ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤

16. እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዕዝራ 7