ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕዝራ 7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ

1. ከእነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት፣ ዕዝራ የሠራያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ

2. የሰሎም ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የአኪጦብ ልጅ፣

3. የአማርያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣

4. የዘራእያ ልጅ፣ የኦዚ ልጅ፣ የቡቂ ልጅ፣

5. የአቢሱ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ፣ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፣

6. ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ። እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ የሕግ መምህር ነበር። የአምላኩ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ የጠየቀውን ሁሉ ንጉሡ ፈቀደለት።

7. እንደዚሁም አንዳንድ እስራኤላውያን፣ ከካህናት፣ ከሌዋውያን፣ ከመዘምራን፣ ከበር ጠባቂዎችና ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ጋር በመሆን በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሰባተኛው ዓመት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

8. ዕዝራ በንጉሡ ሰባተኛ ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ።

9. መልካሚቱ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ።

10. ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በማድረግ፣ ለእስራኤልም ሥርዐቱንና ሕጉን በማስተማር ራሱን ፈጽሞ ሰጥቶ ነበር።

ንጉሥ አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ

11. እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን ሕግና ትእዛዝ ዐዋቂ ለነበረው ለካህኑና ለመምህሩ ዕዝራ ንጉሥ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

12. ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፤ ለሰማይ አምላክ ሕግ መምህር ለሆነው ለካህኑ ለዕዝራ፤ሰላም ለአንተ ይሁን፤

13. ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖርና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚፈልግ ማንኛውም እስራኤላዊ መሄድ እንዲችል ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

14. በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል።

15. ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤

16. እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ።

17. በዚህም ገንዘብ ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን፣ ከእህል ቊርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቊርባኖቻቸው ጋር መግዛት እንዳለብህ አትርሳ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ አቅርብ።

18. ከዚህ የሚቀረውንም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ አይሁድ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ደስ ለሚላችሁ ነገር ሁሉ አውሉት።

19. ለአምላክህ ቤተ መቅደስ በዐደራ የተሰጠህንም ዕቃ ሁሉ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ።

20. ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።

21. በኤፍራጥስ ማዶ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ፣ የሰማይ አምላክ ሕግ መምህር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት እኔ ንጉሥ አርጤክስስ እነሆ አዝዣለሁ፤

22. እስከ አንድ መቶ መክሊት ብር፣ እስከ አንድ መቶ ቆሮስ ስንዴ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ የወይራ ዘይትና የሚፈለገውን ያህል ጨው ስጡት።

23. የሰማይ አምላክ የሚያዘው ሁሉ፣ ለሰማይ አምላክ ቤተ መቅደስ በፍጹም ትጋት ይደረግ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ለምን ቊጣ ይውረድ?

24. ደግሞም በካህናቱ፣ በሌዋውያኑ፣ በመዘምራኑ፣ በበር ጠባቂዎቹ፣ በቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ወይም በሌሎቹ በዚህ በእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞች ላይ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻ ለመጣል ሥልጣን እንደ ሌላችሁ ይህን ዕወቁ።

25. አንተም ዕዝራ ከአምላክህ እንደ ተሰጠህ ጥበብ መጠን፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ የሚያውቁ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፤ ሕጉን የማያውቅ ሰው ቢኖር፣ አንተ ራስህ አስተምረው።

26. ለአምላክህ ሕግና ለንጉሡ ሕግ የማይታዘዝ ማንኛውም ሰው፣ የሞት ወይም የስደት ወይም የንብረት መወረስ ወይም የእስራት ቅጣት ይፈጸምበት።

27. በኢየሩሳሌም የሚገኘው የእግዚአብሔር ቤት በዚህ ሁኔታ እንዲከበር ይህን በንጉሡ ልብ ያኖረ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤

28. እንዲሁም በንጉሡ፣ በአማካሪዎቹና በኀያላን ሹሞቹ ፊት ሁሉ ሞገስን የሰጠኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ የአምላኬ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ስለ ነበረች፣ አብረውኝ እንዲሄዱ ከእስራኤል መካከል የታወቁ ሰዎችን ለመሰብሰብ ብርታት አገኘሁ።