ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 42:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት መሄድ እንዳለብንና ምን ማድረግ እንደሚገባን እንዲነግረን ጸልይልን።”

4. ነቢዩ ኤርምያስም፣ “ሰምቻችኋለሁ፤ እንዳላችሁት ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር በእርግጥ እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔር ያለኝን ሁሉ አንዳች ሳላስቀር እነግራችኋለሁ” አላቸው።

5. እነርሱም ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “እግዚአብሔር አምላክህ በአንተ በኩል የሚለውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፣ እግዚአብሔር ራሱ በእኛ ላይ እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን።

6. አምላካችንን እግዚአብሔርን በመታዘዝ መልካም ይሆንልን ዘንድ ነገሩ ቢስ ማማንም ባይስማማንም፣ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንታዘዛለን።”

7. ከዐሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።

8. ስለዚህ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንንና፣ ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጦር መኰንኖች ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡን ሁሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ጠርቶ፤

9. እንዲህ አላቸው፤ “ልመናችሁን በፊቱ እንዳቀርብ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

10. ‘ባመጣሁባችሁ ጥፋት አዝኛለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፤ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።

11. አሁን የሚያስፈራችሁን የባቢሎንን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ፤ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ ይላል እግዚአብሔር፤

12. እርሱ እንዲምራችሁና ወደ አገራችሁ እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።’

13. “እናንተ ግን፤ ‘በዚህች ምድር አንቀመጥም’ ብትሉና አምላካችሁን እግዚአብሔርን ባትታዘዙ፣

14. ደግሞም፣ ‘ጦርነት ወደማናይበት፣ የመለከት ድምፅ ወደማንሰማበትና ወደማንራብበት ወደ ግብፅ ምድር ሄደን በዚያ እንኖራለንጰ ብትሉ፣

15. እንግዲህ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ግብፅ ለመሄድ ወስናችሁ እዚያ ለመቀመጥ ብትሄዱ፣

16. የፈራችሁት ሰይፍ በዚያ ያገኛችኋል፤ የሠጋችሁበት ራብ እስከ ግብፅ ድረስ ተከትሎአችሁ ይመጣል፤ በዚያም ትሞታላችሁ።

17. በዚያም ለመኖር ወደ ግብፅ ለመሄድ የወሰኑ ሁሉ በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር በእርግጥ ይሞታሉ፤ ከማመጣባቸውም ጥፋት አንድ እንኳ የሚተርፍ ወይም የሚያመልጥ አይገኝም።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 42