ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኤርምያስ 30:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘የፍርሀትና የሽብር ጩኸት ተሰምቶአል፤ሰላምም የለም።

6. እስቲ ጠይቁ፤ ተመልከቱም፤ወንድ መውለድ ይችላል?ታዲያ ወንድ ሁሉ ምጥ እንደ ያዛት ሴት፣እጁን በሆዱ ላይ አድርጎ፣የሰውስ ሁሉ ፊት ጠቍሮ የማየው ለምንድን ነው?

7. ያ ቀን ምንኛ አስጨናቂ ይሆናል!እንደዚያም ያለ አይኖርም፤ለያዕቆብ የመከራ ጊዜ ነው፤ነገር ግን ይተርፋል።

8. “ ‘በዚያን ቀን’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤‘በጫንቃቸው ላይ ያለውን ቀንበር እሰብራለሁ፤እስራታቸውንም እበጥሳለሁ፤ከእንግዲህ ባዕዳን አይገዙአቸውም።

9. ነገር ግን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር፣ለማስነሣላቸውም ለንጉሣቸው፣ለዳዊት ይገዛሉ።

10. “ ‘ስለዚህ፤ አገልጋዬ ያዕቆብ ሆይ፤ አትፍራ፤እስራኤል ሆይ፤ አትደንግጥ፤’ይላል እግዚአብሔር፤‘አንተን ከሩቅ አገር፣ዘርህንም ከተማረኩበት ምድር እታደጋለሁ፤ያዕቆብ ተመልሶ በሰላምና በርጋታ ይቀመጣል፣የሚያስፈራውም አይኖርም።

11. እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ አድንሃለሁም፣ይላል እግዚአብሔር፤‘በአሕዛብ መካከል በትኜሃለሁ፤እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤አንተን ግን ሙሉ በሙሉ አላጠፋህም፤በመጠኑ እቀጣሃለሁ እንጂ፣ያለ ቅጣት አልተውህም።

12. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ ‘ስብራትህ የማይጠገን፣ቍስልህም የማይድን ነው።

13. የሚሟገትልህ ሰው የለም፤ለቍስልህ መድኃኒት አይኖርም፤ፈውስም አታገኝም።

14. ወዳጆችህ ሁሉ ረስተውሃል፤ስለ አንተም ግድ የላቸውም።ጠላት እንደሚመታ መታሁህ፤እንደ ጨካኝም ቀጣሁህ፤በደልህ ታላቅ፣ኀጢአትህም ብዙ ነውና።

15. ፈውስ ለማይገኝለት ሕመምህ፣ስለቍስልህ ለምን ትጮኻለህ?በደልህ ታላቅ፣ ኀጢአትህም ብዙ ስለ ሆነ፣እነዚህን ሁሉ አድርጌብሃለሁና።

16. “ ‘ነገር ግን አሟጠው የበሉህ ሁሉ እንደዚያው ይበላሉ፤ጠላቶችህ ሁሉ ለምርኮ ዐልፈው ይሰጣሉ፤የሚዘርፉህ ይዘረፋሉ፤የሚበዘብዙህም ሁሉ ይበዘበዛሉ።

17. አንተን ግን መልሼ ጤነኛ አደርግሃለሁ፤ቍስልህንም እፈውሳለሁ፤’ይላል እግዚአብሔር።“ ‘የተናቀች፣ማንም የማይፈልጋት ጽዮን” ብለውሃልና።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኤርምያስ 30