ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢያሱ 11:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. እነዚህም ሰራዊታቸውን ሁሉ እጅግ ብዙ ከሆኑ ፈረሶችና ሠረገሎች ጋር ይዘው ወጡ፤ የሰራዊቱም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበር።

5. እነዚህ ሁሉ ነገሥታት እስራኤልን ለመውጋት ኀይላቸውን አስተባብረው በማሮን ውሃ አጠገብ በአንድነት ሰፈሩ።

6. እግዚአብሔር ኢያሱን፣ “እነዚህን ሁሉ ነገ በዚች ሰዓት እንደ ሙት አድርጌ፣ በእስራኤል እጅ አሳልፌ ስለምሰጣቸው አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ትቈርጣለህ፤ ሠረገሎቻቸውንም ታቃጥላለህ” አለው።

7. ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ ሁሉ በድንገት ወደ ማሮን ውሃ መጥተው ወጓቸው።

8. እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ስለሰጣቸው ድል አደረጓቸው፤ በታላቂቱ ሲዶና መንገድ መጨረሻ እስከ ማስሮን፣ በስተ ምሥራቅም እስከ ምጽጳ ሸለቆ ድረስ አሳደዷቸው፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።

9. ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የፈረሶቻቸውን ቋንጃ ቈረጠ፤ ሠረገሎቻቸውንም አቃጠለ።

10. በዚያን ጊዜም ኢያሱ ወደ ኋላ ተመልሶ አጾርን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለው፤ አጾርም ቀድሞ በእነዚህ ሁሉ መንግሥታት ላይ የበላይነት ነበራት።

11. በውስጧ ያሉትን ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ እስትንፋስ ካለው ፍጡር አንድ እንኳ ሳያስቀሩ ሁሉንም ደመሰሱ፤ ራሷን አሦርንም በእሳት አቃጠሏት።

12. ኢያሱ እነዚህን የነገሥታት ከተሞች በሙሉና ነገሥታታቸውን ሁሉ ያዘ፤ በሰይፍም ስለት ፈጃቸው፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ባዘዘውም መሠረት ፈጽሞ ደመሰሳቸው።

13. ያም ሆኖ ግን ኢያሱ ካቃጠላት ከአጾር በስተቀር፣ እስራኤላውያን በየተራራው ላይ ያሉትን ከተሞች አላቃጠሉም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢያሱ 11