ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 66:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ምድርም የእግሬ ማረፊያ ናት፤ታዲያ የምትሠሩልኝ ቤት፣የማርፍበትስ ስፍራ የቱ ነው?

2. እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን?እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?”ይላል እግዚአብሔር።“ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።

3. ነገር ግን ወይፈን የሚሰዋልኝ፣ሰው እንደሚገድል ነው፤የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል።

4. ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና።በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤የሚያስከፋኝንም መረጡ።”

5. እናንት በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤“እናንት ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣‘እስቲ እግዚአብሔር ይክበርና፣የእናንተን ደስታ እንይ’ አሏችሁ፤ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።

6. ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ!ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ!ይኸውም የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።

7. “ከማማጧ በፊት፣ትወልዳለች፤በምጥ ጣር ከመያዟ በፊት፣ወንድ ልጅ ትገላገላለች።

8. እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል?እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል?አገር በአንድ ጀምበር ይፈጠራልን?ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል?ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።

9. ሊወለድ የተቃረበውን፣እንዳይወለድ አደርጋለሁን?” ይላል እግዚአብሔር።“በሚገላገሉበት ጊዜስ፣ማሕፀን እዘጋለሁን?” ይላል አምላክሽ።

10. “ወዳጆቿ የሆናችሁ ሁሉ፣ከኢየሩሳሌም ጋር ደስ ይበላችሁ፤ስለ እርሷም ሐሤት አድርጉ፤ለእርሷ ያለቀሳችሁ ሁሉ፣ከእርሷ ጋር እጅግ ደስ ይበላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 66