ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ኢሳይያስ 10:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. የድኾችን መብት ለሚገፉ፣የተጨቈነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!

3. በምትጐበኙበት ቀን ምን ይውጣችኋል?ጥፋት ከሩቅ ሲመጣስ ምን ትሆናላችሁ?ርዳታን ለማግኘትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ?ሀብታችሁንስ የት ታገኙታላችሁ?

4. ከእስረኞች ጋር ከመርበትበት፣ከታረዱትም ጋር ከመጣል በቀር ምንም አይተርፋችሁም።ይህም ሁሉ ሆኖ፣ ቍጣው ገና አልበረደም።እጁም እንደ ተዘረጋ ነው።

5. “የቍጣዬ በትር ለሆነ፣የመቅሠፍቴም ዱላ በእጁ ላለው ለአሦራዊው ወዮለት!

6. ሀብታቸውን እንዲዘርፍ፣ ምርኮን እንዲያግበሰብስ፣እንደ መንገድ ላይ ጭቃም እንዲረግጣቸው፣አምላክ በሌለው ሕዝብ ላይ እልከዋለሁ፣በሚያስቈጣኝም ሕዝብ ላይ እሰደዋለሁ።

7. እርሱ ግን እንዲህ አላሰበም፤በልቡም ይህ አልነበረም፤ነገር ግን ዕቅዱ ለማጥፋት፣ብዙ ሕዝቦችንም ለመደምሰስ ነበር።

8. እንዲህም ይል ነበር፤‘የጦር አዛዦቼ በሙሉ ነገሥታት አይደሉምን?

9. ካልኖ እንደ ከርከሚሽ፣ሐማት እንደ አርፋድ፣ሰማርያስ እንደ ደማስቆ አይደሉምን?

10. የጣዖታትን መንግሥታት፣ምስሎቻቸው ከኢየሩሳሌምና ከሰማርያ መንግሥታት የሚበልጡትን እጄ እንደ ያዘች ሁሉ፣

11. በሰማርያና በጣዖቶቿ ያደረግሁትን፣በኢየሩሳሌምና በተቀረጹ ምስሎቿስ እንዲሁ አላደርግምን?።”

12. ጌታ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም ላይ የሚያደርገውን ሁሉ ከፈጸመ በኋላ፣ እንዲህ ይላል የአሦርን ንጉሥ ስለ ልቡ ትዕቢትና ስለ ንቀት አመለካከቱ እቀጣዋለሁ፤

13. የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፤“ ‘ይህን ሁሉ ያደረግሁት በክንዴ ብርታት ነው፤ደግሞም በጥበቤ አስተዋይ ነኝና።የመንግሥታትን ድንበር አፈረስሁ፤ሀብታቸውን ዘረፍሁ፤ነገሥታታቸውን እንደ አንድ ኀያል ሆኜ አዋረድሁ።

14. ሰው እጁን ወደ ወፍ ጎጆ እንደሚሰድ፣እኔም እንዲሁ እጄን ወደ መንግሥታት ሀብት ሰደድሁ፤ሰዎች የተተወ ዕንቍላል እንደሚሰበስቡ፣እኔም እንዲሁ ምድርን ሁሉ ሰበሰብሁ፤ክንፉን ያራገበ የለም፤አፉንም ከፍቶ የጮኸ አልነበረም።’ ”

15. መጥረቢያ በሚቈርጥበት ሰው ላይ ይኵራራልን?መጋዝስ በሚስበው ላይ ይታበያልን?በትር በሚያነሣው ሰው ላይ ራሱን እንደሚነቀንቅ፣ዘንግም ራሱን ዕንጨት እንዳልሆነ አድርጎ እንደሚኵራራ ነው።

16. ስለዚህ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣በፈረጠሙ ጦረኞቹ ላይ የሚያከሳ በሽታ ይልካል፤ከክብሩም በታች እንደ ነበልባል የሚንቦገቦግ እሳትይለኰሳል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ኢሳይያስ 10