ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

አስቴር 4:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. መርዶክዮስ የተደረገውን ሁሉ ባወቀ ጊዜ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ከዚያም ማቅ ለብሶ፣ በራሱ ላይ ዐመድ ነስንሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ አምርሮ እየጮኸ ወደ ከተማዪቱ መካከል ወጣ።

2. ማቅ የለበሰ እንዲገባ ስለማይፈቀድለት፣ የሄደው እስከ ንጉሡ በር ድረስ ብቻ ነበር።

3. የንጉሡ ዐዋጅና ትእዛዝ በደረሰበት አውራጃ ሁሉ፣ በአይሁድ መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ ጾሙ፤ አለቀሱ፤ ጮኹም። ብዙዎቹም ማቅና ዐመድ ላይ ተኙ።

4. የአስቴር ደንገጡሮችና ጃንደረቦች መጥተው ስለ መርዶክዮስ በነገሯት ጊዜ፣ እጅግ አዘነች፤ እርሷም በማቁ ፈንታ የሚለብሰውን ልብስ ላከችለት፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም።

5. ከዚያም አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች መካከል እርሷን እንዲያገለግል የተመደበውን ሀታክን ጠርታ፣ መርዶክዮስ ምን ችግር እንደ ገጠመውና ስለምንስ እንደዚህ እንደሆነ እንዲያጣራ ላከችው።

6. ስለዚህ ሀታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ከተማዪቱ አደባባይ ወደ መርዶክዮስ ወጣ።

7. መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው።

8. አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ አስቴር 4