ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሰቆቃወ 1:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣እንዴት የተተወች ሆና ቀረች!በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች!በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣አሁን ባሪያ ሆናለች።

2. በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤እንባዋ በጉንጮቿ ላይ ይወርዳል፤ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣የሚያጽናናት ማንም የለም፤ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤ጠላቶቿም ሆነዋል።

3. በመከራና በመረገጥ ብዛትይሁዳ ተማርካ ሄደች፤በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤የምታርፍበትንም ስፍራ አጣች፤በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት።

4. የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤ካህናቷ ይቃትታሉ፤ደናግሏ ክፉኛ አዝነዋል፤እርሷም በምሬት ትሠቃያለች።

5. ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤ጠላቶቿ ተመችቶአቸዋል፤ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣ እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል።ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣ወደ ግዞት ሄደዋል።

6. የጽዮን ሴት ልጅ፣ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቶአታል፤መሳፍንቶቿ፣መሰማሪያ እንዳጣ ዋልያ ናቸው፤በአሳዳጆቻቸው ፊት፣በድካም ሸሹ።

7. በተጨነቀችባቸውና በተንከራ ተተችባቸው ቀናት፣ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣ሀብት ሁሉ ታስባለች፤ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣የረዳት ማንም አልነበረም፤ጠላቶቿ ተመለከቷት፤በመፈራረሷም ሣቁ።

8. ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤እርሷ ራሷ ታጒረመርማለች፤ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች።

9. ርኵሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤የሚያጽናናትም አልነበረም፤“እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬንተመልከት፤ጠላት ድል አድርጎአልና!”

10. በሀብቷ ሁሉ ላይ፣ጠላት እጁን ዘረጋ፤ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ፣የከለከልሀቸው፣ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች።

11. እንጀራ በመፈለግ፣ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤በሕይወት ለመኖር፣የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤እኔ ተዋርጃለሁና።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሰቆቃወ 1