ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

መሳፍንት 14:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. እንቈቅልሹን ካልፈታችሁልኝ ግን ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳውን የክት ልብስ እናንተ ትሰጡኛላችሁ።”እነርሱም፣ “በል እንቈቅልሽህን ንገረንና እንስማው” አሉት።

14. ሳምሶንም፣“ከበላተኛው መብል፣ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው።እነርሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቈቅልሹን መፍታት አልቻሉም ነበር።

15. በአራተኛው ቀን የሳምሶንን ሚስት፣ “የእንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን፤ ጠርታችሁ የጋበዛችሁን ልትዘርፉን ነው?” አሏት።

16. ከዚያ የሳምሶን ሚስት ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ከፊቱ በመቅረብ፣ “ለካስ ትጠላኛለህ! በእርግጥ አትወደኝም” አለችው።እርሱም፣ “ይህን ለአባቴም ሆነ ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት።

17. ሚስቱም በሰርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ እያለቀሰች ጨቀጨቀችው፤ አጥብቃ ስለ ነዘነዘችውም በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርሷም በበኩሏ የእንቈቅልሹን ፍች ለሕዝቧ ነገረች።

18. በሰባተኛው ቀን ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት የከተማው ሰዎች፣“ከማር የጣፈጠ ምን ተገኝቶ?ከአንበሳስ ወዲያ ብርቱ ከየት መጥቶ!” አሉት።ሳምሶንም መልሶ፣“በጊደሬ ባላረሳችሁ፣እንቈቅልሼንም ባልፈታችሁ” አላቸው።

19. ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል ሠላሳውን ገደለ፤ ያላቸውንም ከገፈፈ በኋላ ልብሶቻቸውን አምጥቶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው። በቍጣ እንደነደደም ተነሥቶ ወደ አባቱ ቤት ወጣ።

20. የሳምሶንም ሚስት ለሚዜው ተዳረች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ መሳፍንት 14