ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 18:4-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “አስቀድመህ ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ጠይቅ” አለው።

5. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት ልሂድን ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ሂድ” ብለው መለሱለት።

6. ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ።

7. የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት አንድ ሰው አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ ደግ ትንቢት ስለማይናገር እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚካያ ነው” ሲል መለሰ።ኢዮሳፍጥም፣ “ንጉሥ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው።

8. የእስራኤልም ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “ሂድና የይምላን ልጅ ሚካያን በፍጥነት አምጣው” አለው።

9. የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

10. የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ” አለ።

11. ሌሎቹ ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በሬማት ገለዓድ ላይ አደጋ ጣልባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12. ሚካያን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ እየተነበዩ ነው፤ ያንተም ቃል እንደቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውን ተናገር” አለው።

13. ሚካያ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እናገራለሁ” አለ።

14. እዚያ በደረሰም ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚካያ ሆይ፤ ሬማት ዘገለዓድን ለመውጋት እንሂድ ወይስ ልቅር?” ሲል ጠየቀው።እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ አልፈው ይሰጣሉና” አለው።

15. ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 18