ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 23:21-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ።

22. እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም።

23. በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተከበረ።

24. ከዚህም በቀር ኢዮስያስ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን፣ የየቤተ ሰውን አማልክት፣ ጣዖታትን እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የተገኙትን ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ አስወገደ፤ ይህን ያደረገውም ካህኑ ኬልቅያስ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈው የሕጉ ቃል ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው።

25. በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ፣ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ፣ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ ፈጽሞ አልተነሣም።

26. ይህም ሆኖ እንኳ ለቊጣ እንዲነሣሣ ምናሴ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተነሣ፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከአስፈሪው ቊጣው ገና አልበረደም ነበር።

27. ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “እስራኤልን እንዳስወገድሁ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ብዬ የተናገር ሁለትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ” አለ።

28. በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

29. ኢዮስያስ ንጉሥ በነበረበት ዘመን የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ የአሦርን ንጉሥ ለመርዳት ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጥቶ ነበር፤ ንጉሥ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሆኖም ፈርዖን ኒካዑ ፊት ለፊት ገጥሞት መጊዶ ላይ ገደለው።

30. የኢዮስያስም አገልጋዮች ከመጊዶ ሬሳውን በሠረገላ ወደ ኢየሩሳሌም አምጥተው በገዛ መቃብሩ ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፤ ቀብተውም በአባቱ እግር አነገሡት።

31. ኢዮአክስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሦስት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሦስት ወር ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

32. አባቶቹ እንዳደረጉ ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

33. በኢየሩሳሌም ተቀምጦ እንዳይ ገዛም ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ሪብላ በምትባል ቦታ በሰንሰለት አሰረው፤ በይሁዳም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ግብር ጣለበት።

34. ፈርዖን ኒካዑ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ እግር አነገሠው፤ ኤልያቄም የተባለ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ነገር ግን ኢዮአክስን በምርኮ ወደ ግብፅ ወሰደው፤ እርሱም በዚያ ሞተ።

35. ኢዮአቄምም ፈርዖን ኒካዑ የጠየቀውን ብርና ወርቅ ከፈለ፤ ይህን ለማድረግም የመሬት ግብር ጣለ፤ የአገሩም ሰዎች እንደ ገቢው መጠን ብሩንና ወርቁን እንዲከፍሉ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 23