ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 19:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ።

2. ከዚያም የቤተ መንግሥቱን አዛዥ ኤልያቄምን፣ ጸሓፊውን ሳምናስንና ዋና ዋናዎቹን ካህናት ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ሁሉንም ላካቸው።

3. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ የሚለው ይህ ነው፤ ‘እንግዲህ ይህች ዕለት የመከራ፣ የዘለፋና የውርደት ቀን ናት፤ ይህችም ቀን ልጆች ሊወለዱ ምጥ እንዳፋፋመበት፣ ነገር ግን ለመገላገል ዐቅም እንደታጣበት ሰዓት ናት።

4. ሕያው እግዚአብሔርን ያንቋሽሽ ዘንድ በጌታው በአሦር ንጉሥ የተላከውን የጦር አዛዡን ቃል ሁሉ እግዚአብሔር አምላክህ ሰምቶ ይሆናልና፣ ስለሰማውም ቃል እግዚአብሔር እንዲገሥጸው በሕይወት ስለተረፉት ወገኖቻችን እባክህ ጸልይ።”

5. የንጉሥ ሕዝቅያስ ሹማምት ወደ ኢሳይያስ በመጡ ጊዜ፣

6. ኢሳይያስ እንዲህ አላቸው፤ “ለጌታችሁ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ ‘እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች በእኔ ላይ የወረወሯቸውን የስድብ ቃላት በመስማትህ አትፍራ።

7. እነሆ፣ አንድ ዐይነት መንፈስ አሳድርበታለሁ፤ የሆነ ወሬም ሲሰማ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ እዚያም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርገዋለሁ።’ ”

8. የጦር አዛዡም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ትቶ መሄዱን ሲሰማ ተመለሰ፤ ንጉሡንም ልብናን ሲወጋ አገኘው።

9. በዚህም ጊዜ የግብፅ ንጉሥ ኢትዮጵያዊው ቲርሐቅ፣ ሊወጋው በመገሥገሥ ላይ መሆኑን ሰናክሬም ሰማ፤ ስለዚህ ወደ ሕዝቅያስ እንደ ገና እንዲህ ሲል መልእክተኞች ላከ፤

10. “ሂዱና ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘የምትመካበት አምላክ፣ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” በማለት እንዳያታልልህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 19