ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 23:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. እርሱ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድልን ሰጠ። የሸሸውም ሰራዊት ወደ ኤልዔዘር የተመለሰው የተገደሉትን ሰዎች ለመግፈፍ ብቻ ነበር።

11. ከእርሱም ቀጥሎ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ፣ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤

12. ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጠ።

13. በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ።

14. በዚያም ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተልሔም ነበረ፤

15. ዳዊትም በናፍቆት፣ “በቤተልሔም በር አጠገብ ካለችው ጒድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ።

16. ስለዚህ ሦስቱ ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፣ በቤተልሔም በር አጠገብ ካለችው ጒድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አድርጎ አፈሰሰው፤

17. “እርሱም፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” አለ፤ ዳዊትም ሊጠጣው አልፈለገም። እንግዲህ ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር።

18. የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ እርሱም ዝናን ያተረፈ ሰው ነበረ።

19. አቢሳ ከሦስቱ ይልቅ እጅግ የከበረ አልነበረምን? ከእነርሱ እንደ አንዱ ባይሆንም አለቃቸው ነበረ።

20. የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ እርሱም ሁለት በጣም የታወቁ የሞዓብን ሰዎች ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጒድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፤

21. ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብፃዊ ገድሎአል፤ ግብፃዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም፣ በናያስ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ወደ እርሱ ሄደ፤ ከግብፃዊውም እጅ ጦሩን በመንጠቅ በገዛ ጦሩ ገደለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 23