ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 11:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ዳዊት፣ “ኦርዮን ወደ ቤቱ አልሄደም” መባሉን ሲሰማ ኦርዮን፣ “ከመንገድ ገና አሁን መግባትህ አይደለምን? ወደ ቤትህ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

11. ኦርዮም ዳዊትን፣ “ታቦቱ፣ እስራኤልና ይሁዳ በድንኳን ሆነው፣ ጌታዬ ኢዮአብና የጌታዬም ሰዎች አውላላ ሜዳ ላይ ሰፍረው፣ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ከሚስቴ ጋር ለመተኛት እንዴት ወደ ቤቴ እሄዳለሁ? እንዲህ ያለውን ነገር እንደማላደርገው በነፍስህ እምላለሁ” አለው።

12. ከዚያም ዳዊት፣ “እንግዲያውስ ዛሬ እዚህ እደርና ነገ አሰናብትሃለሁ” አለው። ስለዚህ ኦርዮን በዚያ ዕለትና በማግስቱ እዚያው ኢየሩሳሌም ቈየ።

13. በማግስቱም ዳዊት ራሱ ባለበት ግብዣ አድርጎለት በላ፤ ጠጣ፤ አሰከረውም፤ ሲመሽም ኦርዮን በምንጣፉ ላይ ለመተኛት የጌታው አሽከሮች ወዳሉበት ወጥቶ ሄደ እንጂ ወደ ቤቱ አልወረደም።

14. ሲነጋም ዳዊት ለኢዮአብ ደብዳቤ ጽፎ በኦርዮን እጅ ላከለት፤

15. በደብዳቤውም ላይ፣ “ኦርዮ ውጊያው በተፋፋመበት ግንባር መድበው፤ ከዚያም ተወግቶ እንዲሞት ትታችሁት ሽሹ” ብሎ ጻፈ።

16. ስለዚህም ኢዮአብ ከተማዪቱን በከበባት ጊዜ፣ እጅግ ጠንካራ ተከላካዮች እንዳሉበት በሚያውቀው ግንባር ኦርዮን መደበው።

17. የከተማዪቱም ሰዎች ወጥተው ከኢዮአብ ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ ከዳዊት ሰራዊት ውስጥ ጥቂቶቹ ወደቁ፤ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮም ሞተ።

18. ኢዮአብም በጦርነቱ የሆነውን ሁሉ ለዳዊት ላከ።

19. መልእክተኛውንም እንዲህ አለው፤ “ይህን የጦርነቱን ወሬ ለንጉሡ ከነገርኸው በኋላ፣

20. ንጉሡ በቍጣ ቱግ ብሎ ‘ለመዋጋት ስትሉ ይህን ያህል ወደ ከተማዪቱ የተጠጋችሁት ስለምንድን ነው? ከግንቡ ቅጥር በላይ ፍላጻ እንደሚሰዱባችሁ አታውቁም ኖሮአል?

21. የይሩቤሼትን ልጅ አቤሜሌክን የገደለው ማነው? በቴቤስ ከግንብ ቅጥር የወፍጮ መጅ ለቃበት የገደለችው አንዲት ሴት አይደለችምን? ታዲያ እናንተስ ወደ ግንቡ ቅጥር ይህን ያህል የተጠጋችሁት ለምንድን ነው?’ በማለት ቢጠይቅህ፣ አንተም መልሰህ፣ ‘አገልጋይህ ኬጢያዊው ኦርዮም ሞቶአል’ ብለህ ንገረው።”

22. ስለዚህ መልእክተኛው ተነሥቶ ሄደ፤ እዚያ እንደ ደረሰም፣ ከኢዮአብ የተቀበለውን መልእክት በሙሉ ለዳዊት ነገረው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 11