ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ሳሙኤል 1:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ በመመለስ፣ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቈየ።

2. በሦስተኛውም ቀን የተቀደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም፣ ወደ መሬት ለጥ ብሎ በአክብሮት እጅ ነሣ።

3. ዳዊትም፣ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር ሸሽቼ መምጣቴ ነው” በማለት መለሰለት።

4. ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ።

5. ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው።

6. ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት፤

7. ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም፣ ‘ምን ልታዘዝ’ አልሁ።

8. “እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፤“እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት።

9. “ከዚያም፣ ‘እኔ በሞት ጣር ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ።

10. “መቼም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፣ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፤ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።”

11. ከዚያም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ።

12. ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፣ ለእግዚአብሔር ሰራዊትና ለእስራኤል ቤት አዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ፤ የወደቁት በሰይፍ ነበርና።

13. ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም፣ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ሳሙኤል 1