ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ሳሙኤል 14:28-40 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

28. ከዚያም አንዱ ወታደር፣ “አባትህ ሰራዊቱን፣ ‘ዛሬ እህል የሚቀምስ ማናቸውም ሰው የተረገመ ይሁን!” በማለት በጽኑ መሓላ አስሮአል። ሰው ሁሉ የተዳከመው በዚሁ ምክንያት ነው” አለው።

29. ዮናታንም እንዲህ አለ፤ “አባቴ በምድሪቱ ላይ ችግር ፈጥሮአል፤ ከዚህ ማር ጥቂት በቀመስሁ ጊዜ ዐይኔ እንዴት እንደ በራ ተመልከቱ።

30. ሕዝቡ ከጠላቶቻቸው እጅ ከወሰዱት ምርኮ ዛሬ በልተው ቢሆን ኖሮ ምንኛ በተሻለ ነበር፤ የተገደሉትም ፍልስጥኤማውያን ቊጥር ከዚህ በበለጠ ነበር።”

31. በዚያች ዕለት እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያንን ከማክማስ እስከ ኤሎን ድረስ ከመቷቸው በኋላ እጅግ ዝለው ነበር።

32. በምርኮው ላይ ተረባርበው በጉን፣ በሬውንና ጥጃውን በመውሰድ በመሬት ላይ ዐርደው ሥጋውን ከነደሙ በሉት።

33. ከዚያም ለሳኦል፣ “እነሆ፤ ሕዝቡ ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን እየበደለ ነው” ተብሎ ተነገረው።ሳኦልም፣ “ሕግ ተላልፋችኋል፤ በሉ አንድ ትልቅ ድንጋይ አንከባላችሁ አቅርቡልኝ” አለ።

34. እርሱም፣ “በሕዝቡ መካከል እየዞራችሁ፣ ‘እያንዳንዳችሁ በሬዎቻችሁንና በጎቻችሁን አምጡ፤ እዚሁ ዐርዳችሁ ብሉ፤ ነገር ግን ሥጋውን ከነደሙ በመብላት እግዚአብሔርን አትበድሉ’ በሏቸው” አለ።ስለዚህ በዚያች ሌሊት እያንዳንዱ ሰው በሬውን አምጥቶ በዚያ ዐረደው።

35. ሳኦልም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያ ሲሠራም ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።

36. ሳኦልም፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትለን በሌሊት እንውረድና እስኪነጋ ድረስ እንበዝብዛቸው፤ አንድም ሰው በሕይወት አናስ ቀርላቸው” አለ።እነርሱም፣ “መልካም መስሎ የታየህን ሁሉ አድርግ” ብለው መለሱለት።ካህኑ ግን፣ “እዚሁ እግዚአብሔርን እንጠይቅ” አለ።

37. በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “ፍልስጥኤማውያንን ተከትዬ ልውረድን? በእስራኤላውያንስ እጅ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። ነገር ግን እግዚአብሔር በዚያች ቀን አልመለሰለትም።

38. ስለዚህ ሳኦል እንዲህ አለ፤ “የሰራዊቱ መሪዎች ሁላችሁም ወደዚህ ቅረቡ፤ ዛሬ ምን ኀጢአት እንደ ተሠራ እንወቅ።

39. እስራኤልን የታደገ ሕያው እግዚአብሔርን! አድራጊው ልጄ ዮናታን እንኳ ቢሆን መሞት አለበት።” ነገር ግን ከሕዝቡ መካከል የመለሰለት አንድም አልነበረም።

40. ሳኦልም እስራኤላውያንን ሁሉ፣ “እናንተ በዚያ በኩል ቁሙ፤ እኔና ልጄ ዮናታን ደግሞ በዚህ በኩል እንቆማለን” አላቸው።ሰዎቹም፣ “መልካም መስሎ የታየህን አድርግ” ብለው መለሱለት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ሳሙኤል 14