ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 2:9-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስም የተሰጠኝን ጸጋ ባስተዋሉ ጊዜ፣ ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድሄድ ተስማሙ።

10. አጥብቀው ዐደራ ያሉን ድኾችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ ብቻ ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማድረግ ጒጒቴ ነበር።

11. ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ፣ በግልጥ ስቶ ስለ ነበር ፊት ለፊት ተቃወምሁት።

12. አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፣ ከአሕዛብ ጋር ይበላ ነበር፤ እነርሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ወገኖች ፈርቶ ከአሕዛብ ራሱን በመለየት ገሸሽ ማለት ጀመረ፤

13. በርናባስም እንኳ በእነርሱ ግብዝነት እስኪወሰድ ድረስ፣ ሌሎቹም አይሁድ በግብዝነቱ ተባበሩት።

14. ተግባራቸው እንደ ወንጌል እውነት አለመሆኑን በተረዳሁ ጊዜ፣ በሁሉም ፊት ጴጥሮስን እንዲህ አልሁት፤ “አንተ አይሁዳዊ ነህ፤ ሆኖም በአሕዛብ ሥርዐት እንጂ በአይሁድ ሥርዐት አትኖርም፤ ታዲያ አሕዛብ የአይሁድን ሥርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታስገድዳቸዋለህ?

15. “እኛ በትውልዳችን አይሁድ እንጂ፣ ‘ኀጢአተኞች አሕዛብ’ ያልሆን፣

16. ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 2