ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጳውሎስን ሐዋርያት ተቀበሉት

1. ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላም፣ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ በዚህ ጊዜ ከበርናባስ ጋር ነበርሁ፤ ቲቶንም ይዤው ሄጄ ነበር።

2. ካገኘሁትም መገለጥ የተነሣ ወደዚያ ሄድሁ፤ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል ለእነርሱም ገለጥሁላቸው። ይሁን እንጂ፣ ምናልባት በከንቱ እየሮጥሁ ወይም ሮጬ እንዳይሆን በመሥጋት፣ ዋነኞች ለሚመስሉት ብቻ በግል ይህን አስታወቅኋቸው።

3. ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ቢሆንም፣ እንዲገረዝ አልተገደደም ነበር።

4. ይህ ጒዳይ የተነሣው አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ነጻነት ሊሰልሉና ባሪያዎች ሊያደርጉን ወደ እኛ ሾልከው በመግባታቸው ነው።

5. ለእነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ እንኳ አልተገዛንላቸውም፤ ይኸውም፣ የወንጌል እውነት ከእናንተ ጋር ጸንቶ እንዲኖር ነው።

6. ዋነኛ መስለው ስለሚታዩት ሰዎች ማንነት እኔን አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ እነዚህም ሰዎች ለመልእክቴ የጨመሩልኝ ነገር የለም።

7. ነገር ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት ወንጌልን እንዲሰብክ ዐደራ እንደ ተሰጠው፣ እኔም ላልተገረዙት ወንጌልን እንድሰብክ አደራ እንደ ተሰጠኝ ተገነዘቡ፤

8. ጴጥሮስን ለአይሁድ ሐዋርያ እንዲሆን የሠራ እግዚአብሔር፣ በእኔ የአሕዛብ ሐዋርያዊ አገልግሎትም ሠርቶአል።

9. እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስም የተሰጠኝን ጸጋ ባስተዋሉ ጊዜ፣ ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድሄድ ተስማሙ።

10. አጥብቀው ዐደራ ያሉን ድኾችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ ብቻ ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማድረግ ጒጒቴ ነበር።

ጳውሎስ ጴጥሮስን ተቃወመው

11. ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ፣ በግልጥ ስቶ ስለ ነበር ፊት ለፊት ተቃወምሁት።

12. አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፣ ከአሕዛብ ጋር ይበላ ነበር፤ እነርሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ወገኖች ፈርቶ ከአሕዛብ ራሱን በመለየት ገሸሽ ማለት ጀመረ፤

13. በርናባስም እንኳ በእነርሱ ግብዝነት እስኪወሰድ ድረስ፣ ሌሎቹም አይሁድ በግብዝነቱ ተባበሩት።

14. ተግባራቸው እንደ ወንጌል እውነት አለመሆኑን በተረዳሁ ጊዜ፣ በሁሉም ፊት ጴጥሮስን እንዲህ አልሁት፤ “አንተ አይሁዳዊ ነህ፤ ሆኖም በአሕዛብ ሥርዐት እንጂ በአይሁድ ሥርዐት አትኖርም፤ ታዲያ አሕዛብ የአይሁድን ሥርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታስገድዳቸዋለህ?

15. “እኛ በትውልዳችን አይሁድ እንጂ፣ ‘ኀጢአተኞች አሕዛብ’ ያልሆን፣

16. ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና።

17. “በክርስቶስ ለመጽደቅ ስንፈልግ፣ እኛ ራሳችን ኀጢአተኞች መሆናችን ግልጽ ነው፤ ታዲያ ክርስቶስ ኀጢአት እንዲስፋፋ ያደርጋልን? ፈጽሞ አይደለም!

18. ያፈረስሁትን መልሼ የምገነባ ከሆነማ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አረጋግጣለሁ።

19. ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ፣ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቻለሁና።

20. ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።

21. የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነማ፣ ክርስቶስ እንዲያው በከንቱ ሞተ ማለት ነዋ!”