ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ገላትያ 2:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. አጥብቀው ዐደራ ያሉን ድኾችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ ብቻ ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማድረግ ጒጒቴ ነበር።

11. ጴጥሮስ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ፣ በግልጥ ስቶ ስለ ነበር ፊት ለፊት ተቃወምሁት።

12. አንዳንድ ሰዎች ከያዕቆብ ዘንድ ከመምጣታቸው በፊት፣ ከአሕዛብ ጋር ይበላ ነበር፤ እነርሱ በመጡ ጊዜ ግን የተገረዙትን ወገኖች ፈርቶ ከአሕዛብ ራሱን በመለየት ገሸሽ ማለት ጀመረ፤

13. በርናባስም እንኳ በእነርሱ ግብዝነት እስኪወሰድ ድረስ፣ ሌሎቹም አይሁድ በግብዝነቱ ተባበሩት።

14. ተግባራቸው እንደ ወንጌል እውነት አለመሆኑን በተረዳሁ ጊዜ፣ በሁሉም ፊት ጴጥሮስን እንዲህ አልሁት፤ “አንተ አይሁዳዊ ነህ፤ ሆኖም በአሕዛብ ሥርዐት እንጂ በአይሁድ ሥርዐት አትኖርም፤ ታዲያ አሕዛብ የአይሁድን ሥርዐት እንዲከተሉ እንዴት ታስገድዳቸዋለህ?

15. “እኛ በትውልዳችን አይሁድ እንጂ፣ ‘ኀጢአተኞች አሕዛብ’ ያልሆን፣

16. ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ፣ ሕግን በመጠበቅ እንደማይጸድቅ እናውቃለን። ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን እንጸድቅ ዘንድ እኛም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፤ ሕግን በመጠበቅ ማንም አይጸድቅምና።

17. “በክርስቶስ ለመጽደቅ ስንፈልግ፣ እኛ ራሳችን ኀጢአተኞች መሆናችን ግልጽ ነው፤ ታዲያ ክርስቶስ ኀጢአት እንዲስፋፋ ያደርጋልን? ፈጽሞ አይደለም!

18. ያፈረስሁትን መልሼ የምገነባ ከሆነማ ሕግ ተላላፊ መሆኔን አረጋግጣለሁ።

19. ለእግዚአብሔር እኖር ዘንድ፣ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቻለሁና።

20. ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው።

21. የእግዚአብሔርን ጸጋ አላቃልልም፤ ጽድቅ በሕግ በኩል የሚገኝ ከሆነማ፣ ክርስቶስ እንዲያው በከንቱ ሞተ ማለት ነዋ!”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ገላትያ 2