ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮሐንስ 5:24-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. “እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ፣ በላከኝም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።

25. እውነት እላችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።

26. አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው ሁሉ፣ ወልድም በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና፤

27. ወልድ የሰው ልጅ ስለ ሆነም እንዲፈርድ ሥልጣን ሰጥቶታል።

28. “በዚህ አትደነቁ፤ መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፤

29. መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።

30. እኔ ብቻዬን ከራሴ ምንም ማድረግ አልችልም፤ የምፈርደው የምሰማውን ብቻ ነው፤ የላከኝን እንጂ የራሴን ፈቃድ ስለማልሻም ፍርዴ ትክክል ነው።

31. “እኔ ስለ ራሴ ብመሰክር፣ ምስክርነቴ ተቀባይነት አይኖረውም።

32. ስለ እኔ የሚመሰክር ሌላ አለ፤ እርሱ ስለ እኔ የሚሰጠውም ምስክርነት እውነት እንደሆነ ዐውቃለሁ።

33. “ወደ ዮሐንስ ልካችሁ ነበር፤ እርሱም ስለ እውነት መስክሮአል፤

34. እኔ የሰው ምስክርነት የምቀበል አይደለሁም፤ ይህን የምናገረው ግን እናንተ እንድትድኑ ነው።

35. ዮሐንስ እየነደደ ብርሃን የሚሰጥ መብራት ነበረ፤ እናንተም ለጥቂት ጊዜ በብርሃኑ ደስ ልትሰኙ ወደዳችሁ።

36. “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክርነት የላቀ ምስክር አለኝ፤ እንድፈጽመው አብ የሰጠኝ፣ እኔም የምሠራው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ይመሰክራል።

37. የላከኝ አብ ራሱ ስለ እኔ መስክሮአል፤ እናንተም ከቶ ድምፁን አልሰማችሁም፤ መልኩንም አላያችሁም፤

38. የላከውንም ስላላመናችሁ ቃሉ በእናንተ አይኖርም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዮሐንስ 5