ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ትኵረት የሚያስፈልጋቸው ነገሮች

1. ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል።

2. ምክንያቱም በመላእክት በኩል የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነና ማንኛውም መተላለፍና አለመታዘዝ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለ፣

3. እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? ይህ ድነት በመጀመሪያ በጌታ ተነገረ፤ ከእርሱ የሰሙትም ለእኛ አረጋገጡልን።

4. እግዚአብሔርም በምልክት፣ በድንቅና በልዩ ልዩ ታምራት እንዲሁም እንደ ፈቃዱ በታደሉት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ስለ ዚሁ ነገር መስክሮአል።

ኢየሱስ ወንድሞቹን መሰለ

5. ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም ለመላእክት አላስገዛም፤

6. ነገር ግን አንዱ በሌላ ስፍራ እንዲህ ብሎ መስክሮአል፤“ታስታውሰው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?ታስብለትስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው”

7. ከመላእክት ጥቂት አሳነስኸው፤የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፤

8. ሁሉንም ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት።እግዚአብሔር ሁሉን ከበታቹ ሲያስገዛለት፣ ያላ ስገዛለት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር ተገዝቶለት አናይም።

9. ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ጥቂት እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ፣ የሞትን መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖለት እናየዋለን።

10. ሁሉ ነገር ለእርሱና በእርሱ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት፣ የድነታቸውን መሥራች በመከራ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነበር።

11. ሰዎችን የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሰዎች ከአንድ ቤተ ሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው ዐያፍርም፤

12. እንዲህም ይላል፤“ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁ፤በጒባኤም መካከል ምስጋናህን እዘምራለሁ።”

13. እንዲሁም፣“እኔ በእርሱ እታመናለሁ።”ደግሞም እንዲህ ይላል፤“እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች።”

14. ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤

15. እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።

16. እርሱ የመጣው መላእክትን ለመርዳት ሳይሆን፣ የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንደሆነ ግልጽ ነው።

17. ስለዚህ በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት ነው።

18. እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።