ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዕብራውያን 10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያቀረበው መሥዋዕት

1. ሕጉ ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው እንጂ፣ እውነተኛው አካል አይደለም፤ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር ያለ ማቋረጥ የሚቀርበው ተደጋጋሚ መሥዋዕት፣ ለአምልኮ የሚቀርቡትን ሰዎች ፍጹም ሊያደርጋቸው ከቶ አይችልም።

2. ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር።

3. ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤

4. ምክንያቱም የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም።

5. ስለዚህ ክርስቶስ ወደ ዓለም በመጣ ጊዜ እንዲህ ብሎአል፤“መሥዋዕትንና መባን አልፈለግህም፤ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤

6. በሚቃጠል መሥዋዕትና ለኀጢአት በሚቀርብ መሥዋዕት ደስ አልተሰኘህም።

7. በዚያን ጊዜ እንዲህ አልሁ፤ ‘ስለ እኔ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈ፣አምላክ ሆይ፤ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ።’ ”

8. ሕጉ ይህ እንዲደረግ ቢያዝም፣ እርሱ ግን በመጀመሪያ፣ “መሥዋዕትንና መባን፣ የሚቃጠል መሥዋዕትንና ስለ ኀጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልፈለግህም፤ ደስም አልተሰኘህበትም” ይላል።

9. ቀጥሎም፣ “እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ” አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ።

10. በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል።

11. ካህን ሁሉ በየዕለቱ ቆሞ አገልግሎቱን ያከናውናል፤ ኀጢአትን ማስወገድ ከቶ የማይችሉትን እነዚያኑ መሥዋዕቶች ዘወትር ያቀርባል።

12. ይህኛው ካህን ግን አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል፤

13. ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል፤

14. ምክንያቱም በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል።

15. መንፈስ ቅዱስም ስለዚህ ነገር ይመሰክርልናል፤ በመጀመሪያ እንዲህ ይላል፤

16. “ከዚያም በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ይላል ጌታ፤ሕጌን በልባቸው አኖራለሁ፤በአእምሮአቸውም እጽፈዋለሁ።”

17. ደግሞም፣“ኀጢአታቸውንና ዐመፃቸውን፣ከእንግዲህ አላስብም” ይላል።

18. እነዚህ ይቅር ከተባሉ በኋላ ከእንግዲህ ስለ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት አይኖርም።

እስከ መጨረሻው ጸንቶ ስለ መገኘት የቀረበ ጥሪ

19. እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤

20. ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው።

21. በእግዚአብሔር ቤት ላይ የተሾመ ታላቅ ሊቀ ካህናት ስላለን

22. ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ።

23. የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለ ሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ።

24. እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ።

25. አንዳንዶች ማድረጉን እንደተዉት መሰብሰባችንን አንተው፤ ይልቁንም ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን ስታዩ እርስ በርሳችን እንበረታታ።

26. የእውነትን ዕውቀት ከተቀበልን በኋላሆን ብለን በኀጢአት ጸንተን ብንመላለስ፣ ከእንግዲህ ለኀጢአት የሚሆን ሌላ መሥዋዕት አይኖርም፤

27. የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።

28. የሙሴን ሕግ የናቀ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይገደል ነበር።

29. ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል?

30. “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል።

31. በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው።

32. ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን ዐስቡ።

33. አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል።

34. እናንተ ራሳችሁ የተሻለና ለዘወትር የሚኖር ሀብት ያላችሁ መሆናችሁን ስለምታውቁ ለታሰሩት ራራችሁ፤ ንብረታችሁም ሲዘረፍ በደስታ ተቀበላችሁ።

35. ስለዚህ ታላቅ ዋጋ ያለውን መታመናችሁን አትጣሉ።

36. የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽማችሁ የተስፋ ቃሉን እንድትቀበሉ፣ ጸንታችሁ መቆም ያስፈልጋችኋል፤

37. ምክንያቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣“የሚመጣው እርሱ ይመጣል፤ አይዘገይም።

38. ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል፤ወደ ኋላ ቢያፈገፍግ፣ነፍሴ በእርሱ ደስ አትሰኝም።”

39. እኛ ግን አምነው ከሚድኑት ወገን እንጂ፣ ወደ ኋላ አፈግፍገው ከሚጠፉት አይደለንም።