ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 3:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ፈጽሞ አይሆንም! ሰው ሁሉ ሐሰተኛ፣ እግዚአብሔር ግን እውነተኛ ይሁን፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤“ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ፣በፍርድም ፊት ረቺ ትሆናለህ።”

5. የእኛ ዐመፃ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አጒልቶ የሚያሳይ ከሆነ፣ ምን ማለት እንችላለን? እንደ ሰው ለመከራከር ያህል እግዚአብሔር በእኛ ላይ ቊጣውን ማምጣቱ ትክክል አይደለም ሊባል ነውን? እንደ ሰው ሲታሰብ ማለቴ ነው።

6. በርግጥ እንዲህ ሊሆን አይችልም፤ እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ሊፈርድ ይችላል?

7. “የእኔ ውሸተኛ መሆን የእግዚአብሔርን እውነተኛነት የሚያጐላ፣ ክብሩንም የሚጨምርለት ከሆነ፣ ኀጢአተኛ ተብዬ እስካሁን እንዴት ይፈርድብኛል?” በማለት ሊከራከር የሚችል ሰው ይኖር ይሆናል።

8. ይህማ “በጎ እንዲመጣ ክፉ እንሥራ” ይላሉ በማለት አንዳንዶች እንደሚያስወሩብን ነው፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፍርድ ትክክለኛ ነው።

9. እንግዲህ ምን እንላለን? እኛ ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ፣ ሁሉም ከኀጢአት በታች እንደሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋል፤

10. እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ጻድቅ ማንም የለም፤ አንድም እንኳ፤

11. አስተዋይ የለም፤እግዚአብሔርንም የሚሻ አንድም የለም።

12. ሁሉም ተሳስተዋል፤በአንድነት የማይጠቅሙ ሆነዋል፤በጎ የሚያደርግ ማንም የለም፤አንድም እንኳ።”

13. “ጒሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤አንደበታቸው ሽንገላን ያዘወትራል።”“በከንፈሮቻቸው የእባብ መርዝ አለ።”

14. “አፋቸው ርግማንና ምሬት ሞልቶበታል።”

15. “እግራቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣን ነው፤

16. በመንገዳቸው ጥፋትና ጒስቊልና ይገኛል፤

17. የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”

18. “በዐይናቸው ፊት የእግዚአብሔር ፍርሀት የለም።”

19. እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ ለእግዚአብሔር መልስ እንዲሰጥ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ፣ እናውቃለን፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 3