ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 16:13-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. በጌታ ለተመረጠው ለሩፎንና የእኔም እናት ለሆነችው ለእናቱ ሰላምታ አቅርቡልኝ።

14. ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ፣ ለሄሮሜን፣ ለጳጥሮባን፣ ለሄርማን፣ ከእነርሱም ጋር ላሉት ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ።

15. ለፍሌጎን፣ ለዩልያ፣ ለኔርያና ለእኅቱ፣ እንዲሁም ለአልንጦን፣ ከእነርሱም ጋር ላሉት ቅዱሳን ሰላምታ አቅርቡልኝ።

16. በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

17. ወንድሞች ሆይ፤ መለያየትን ከሚፈጥሩትና የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም በጒዞአችሁ መሰናክል ከሚያደርጉት እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ።

18. እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን፣ የራሳቸውን ሆድ ነው፤ በለሰለሰ አንደ በታቸውና በሽንገላ፣ የዋሆችን ያታልላሉ።

19. የእናንተን ታዛዥነት ሁሉም ሰምተዋል፤ በዚህም እኔ እጅግ ተደስቻለሁ። ሆኖም በጎ ስለ ሆነው ነገር ጥበበኞች፣ ክፉ ስለ ሆነውም የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።

20. የሰላም አምላክ፣ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል።የጌታችን የኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

21. አብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ፣ እንዲሁም ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስ፣ ኢያሶንና ሱሲጴጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

22. ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ፣ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ።

23. በመልካም መስተንግዶው እኔና በዚህ የምትገኘዋ መላዋ ቤተ ክርስቲያን ደስ የምንሰኝበት ጋይዮስ፣ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።የከተማዪቱ ግምጃ ቤት ሹም የሆነው ኤርስጦስ፣ ወንድማችንም ቊአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

24. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 16