ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 15:24-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ይህን ዕቅድ ወደ እስጳንያ በምሄድበት ጊዜ ልፈጽመው አስባለሁ። በማልፍበትም ጊዜ ልጐበኛችሁና ከእናንተ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ በጒዞዬ እንደም ትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

25. አሁን ግን በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ነኝ።

26. ምክንያቱም መቄዶንያና አካይያ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል የሚገኙትን ድኾች ለመርዳት ተነሣሥተዋልና።

27. ርዳታ ለማድረግ ወደዋል፤ በርግጥም ባለ ዕዳዎቻቸው ናቸው። አሕዛብ የአይሁድ መንፈሳዊ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ፣ ያገኙትን ምድራዊ በረከት ከአይሁድ ጋር ይካፈሉ ዘንድ የእነርሱ ባለ ዕዳዎች ናቸው።

28. ስለዚህ ሥራውን ከጨረስሁና ይህን ፍሬ መቀበላቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ እግረ መንገዴንም እናንተን አያለሁ።

29. ወደ እናንተም ስመጣ፣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ ዐውቃለሁ።

30. ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የተጋድሎዬ አጋር እንድትሆኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ።

31. በይሁዳ ካሉት ከማያምኑት እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለው አገልግሎቴም በዚያ ባሉት ቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤

32. ይኸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተም ጋር እንድታደስ ነው።

33. የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 15