ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሮሜ 11:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንግዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ተዋቸውን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! እኔ ራሴ ከብንያም ነገድ፣ የአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝ።

2. እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝብ አልጣላቸውም። ኤልያስ በእስራኤል ላይ ክስ ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንዳቀረበ፣ መጽሐፍ ስለ እርሱ ምን እንደሚል አታውቁምን?

3. “ጌታ ሆይ፤ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ሊገድሉኝም ይፈልጋሉ።”

4. እግዚአብሔር የሰጠው መልስ ግን ምን ነበር? “ለበኣል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ።”

5. በአሁኑ ጊዜም እንደዚሁ በጸጋ የተመረጡ ትሩፋን አሉ።

6. እንግዲህ በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም፤ በሥራ ቢሆንማ ኖሮ ጸጋ፣ ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።

7. እንግዲህ ምንድን ነው? እስራኤል አጥብቀው የፈለጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ልባቸው ደነደነ፤

8. እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤“ዐይናቸው እንዳያይ፣ጆሮአቸውም እንዳይሰማ፣እግዚአብሔር እስከዚህ ቀን ድረስ፣የድንዛዜ መንፈስ ሰጣቸው።”

9. ዳዊትም አለ፤“ማእዳቸው አሽክላና ወጥመድ፣ዕንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው።

10. ዐይኖቻቸው እንዳያዩ ይጋረዱ፤ወገባቸውም ለዘላለም ይጒበጥ።”

11. ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይደለም፤ ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቶአል።

12. ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸውምን ያህል ታላቅ በረከትያመጣ ይሆን?

13. አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤

14. ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው።

15. የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

16. በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።

17. ከቅርንጫፎቹ አንዳንዶቹ ቢሰበሩ፣ አንተም የበረሓ ወይራ ሆነህ ሳለ በሌሎቹ መካከል ገብተህ ከተጣበቅህና ከወይራው ዘይት ሥር የሚገኘውን በረከት ተካፋይ ከሆንህ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሮሜ 11