ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 5:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በውስጥና በውጭ በኩል የተጻፈበት፣ በሰባት ማኅተም የታሸገ ጥቅልል መጽሐፍ በቀኝ እጁ ይዞ አየሁ።

2. አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ፣ “ማኅተሞቹን ለመፍታትና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ።

3. ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር፣ ከምድርም በታች መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የሚችል ማንም አልነበረም።

4. እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ።

5. ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቶአል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።

6. ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።

7. እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ።

8. መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግምባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።

9. እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤“መጽሐፉን ልትወስድ፣ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ምክንያቱም ታርደሃል፤በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።

10. ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”

11. ከዚያም ተመለከትሁ፤ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም ሺህ ጊዜ ሺህና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከበው ነበር፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 5