ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ራእይ 13:4-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ሰዎችም ለዘንዶው ሰገዱለት፤ ምክንያቱም ሥልጣኑን ለአውሬው ሰጥቶታል። ደግሞም፣ “አውሬውን የሚመስል ማን ነው? ከእርሱስ ጋር ማን ሊዋጋ ይችላል?” በማለት ለአውሬው ሰገዱለት።

5. አውሬው የትዕቢት ቃል የሚናገርበትና የሚሳደብበት አፍ ተሰጠው፤ አርባ ሁለት ወር በሥልጣን እንዲሠራም ተፈቀደለት።

6. እርሱም እግዚአብሔርን ለመሳደብ እንዲሁም ስሙንና ማደሪያውን፣ በሰማይም የሚኖሩትን ለመሳደብ አፉን ከፈተ።

7. ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድልም እንዲነሣቸው ኀይል ተሰጠው። በነገድ፣ በወገን፣ በቋንቋና በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።

8. ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በታረደው በግ የሕይወት መጽሐፍ ላይ ስሞቻቸው ያልተጻፈ የምድር ሰዎች ሁሉ ለአውሬው ይሰግዳሉ።

9. ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።

10. ማንም የሚማረክ ቢኖር፣እርሱ ይማረካል፤ማንም በሰይፍ የሚገድል ቢኖር፣እርሱ በሰይፍ ይገደላል።ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደሆነ ያስገነዝባል።

11. ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እርሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገር ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ራእይ 13