ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 9:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ።

2. በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።

3. በዚህን ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ።

4. ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ?

5. ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?

6. ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው’ ብሎ፣ ሽባውን፣ ‘ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ’ ” አለው።

7. ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ።

8. ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፣ በፍርሃት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

9. ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ ማስከፈያ ኬላ ተቀምጦ አየ፤ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።

10. ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ሊበሉ ተቀመጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 9