ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 6:20-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤

21. ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።

22. “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።

23. ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን?

24. “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።

25. “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሮአችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን?

26. እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?

27. ለመሆኑ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንዲት ሰዓት መጨመር የሚችል አለን?

28. “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስቲ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም።

29. ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ያን ያህል ክብር የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን እንኳ ከእነዚህ አበቦች እንደ አንዲቱ አልለበሰም።

30. እናንተ እምነት የጐደላችሁ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 6