ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 25:14-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. “የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋዮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤

15. ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጒዞውን ቀጠለ።

16. አምስት ታላንት የተቀበለው ሰውዬ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ አምስት ታላንት አተረፈ፤

17. እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤

18. አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ።

19. “የአገልጋዮቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ።

20. አምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ አምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ! አምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ አምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

21. “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

22. “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው።

23. “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው።

24. “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤

25. ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው።

26. “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ አገልጋይ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሮአል?

27. ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር።

28. “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤

29. ላለው ይጨመርለታል፤ የተትረፈረፈም ይኖረዋል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 25