ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማቴዎስ 20:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “መንግሥተ ሰማይ ለወይኑ ቦታ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ የወጣን የአትክልት ስፍራ ባለቤት ትመስላለች።

2. በቀን አንዳንድ ዲናር ሊከፍላቸው ከተስማሙ በኋላ ሠራተኞቹን በወይኑ ቦታ አሰማራቸው።

3. “ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ በመውጣት ሥራ ፈትተው በገበያ ቦታ የቆሙትን ሌሎች ሰዎች አግኝቶ፣

4. ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ፤ ተገቢውን ክፍያ እሰጣችኋለሁ’ አላቸው፤

5. እነርሱም ሄዱ። “ከቀኑ በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ላይ ወጥቶ ሌሎች የቀን ሠራተኞችን ቀጠረ።

6. ከሰዓት በኋላ በዐሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና፣ ‘ቀኑን ሙሉ ያለ ሥራ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ በማለት ጠየቃቸው።

7. “እነርሱም፣ ‘የሚቀጥረን ሰው ስለ አጣን ነው’ አሉት። “እርሱም፣ ‘እናንተም ሄዳችሁ በወይኔ ቦታ ሥሩ’ አላቸው።

8. “በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሠራተኞቹን ተቈጣጣሪ፣ ‘ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ያሉትን ሠራተኞች በሙሉ ጥራና ደመወዛቸውን ክፈላቸው’ አለው።

9. “በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ገደማ የተቀጠሩት ሠራተኞች ቀርበው፣ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ።

10. በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲቀርቡ ብልጫ ያለው ክፍያ የሚያገኙ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አንዳንድ ዲናር ተከፈላቸው።

11. ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣

12. ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሐይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋር እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት።

13. “እርሱም አንደኛውን ሠራተኛ እንዲህ አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋር ተስማምተህ አልነበረምን?

14. በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ።

15. ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኝነት ያዘህን?’

16. “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”

17. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወስዶ እንዲህ አላቸው፤

18. “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዳችን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለኦሪት ሕግ መምህራን አልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም እንዲሞት ይፈርዱበታል፤

19. እንዲያላግጡበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሣል።”

20. ከዚያም፣ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆቿ ጋር ወደ ኢየሱስ ቀርባ በፊቱ ተንበርክካ እየሰገደች፣ አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማቴዎስ 20