ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 8:26-37 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

27. ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

28. እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት።

29. ቀጥሎም፣ “እናንተሳ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።ጴጥሮስም፤ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው።

30. ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።

31. ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።

32. እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።

33. ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፣ ወደ ኋላዬ ሂድ! አንተ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና” በማለት ገሠጸው።

34. ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤

35. ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል።

36. ሰው ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?

37. ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው?

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 8