ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 3:20-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ።

21. ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቶአል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ።

22. ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።

23. እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል?

24. እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤

25. ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ሊቆም አይችልም።

26. እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል።

27. ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው።

28. እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤

29. ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።”

30. ይህንንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር።

31. ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ በውጭ ቆመውም ሰው ልከውበት አስጠሩት።

32. በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣ “እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃል” አሉት።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ማርቆስ 3