ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6
  7. 7
  8. 8
  9. 9
  10. 10
  11. 11
  12. 12
  13. 13
  14. 14
  15. 15
  16. 16

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ማርቆስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በሌላ ጊዜ ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር።

2. በምክንያት ሊከሱት የሚፈልጉ ሰዎችም በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደሆነ ለማየት ይጠባበቁ ነበር።

3. እርሱም እጁ የሰለለችውን ሰው፣ “በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት ተነሥተህ ቁም” አለው።

4. ኢየሱስም፣ “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነውን ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ።

5. በልባቸው ደንዳናነት አዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸውና ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ!” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም ፍጹም ደኅና ሆነችለት።

6. ፈሪሳውያንም እንዴት ሊያጠፉት እንደሚችሉ ከሄሮድስ ወገን ከሆኑት ጋር መመካከር ጀመሩ።

ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተከተሉ

7. ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤

8. የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ።

9. የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።

10. ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር።

11. ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” በማለት ይጮኹ ነበር።

12. እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መሾም

13. ኢየሱስ ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ።

14. ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፣ ለስብከትም ይልካቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤

15. አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው።

16. የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣

17. ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤

18. እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርቶሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ተቀናቃኙ ስምዖን፣

19. እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

ኢየሱስና ብዔልዜቡል

20. ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ።

21. ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቶአል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ።

22. ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል አድሮበታል፤ አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።

23. እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል?

24. እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤

25. ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ሊቆም አይችልም።

26. እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል።

27. ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው።

28. እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤

29. ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።”

30. ይህንንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር።

የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ

31. ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ በውጭ ቆመውም ሰው ልከውበት አስጠሩት።

32. በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣ “እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃል” አሉት።

33. እርሱም መልሶ፣ “እናቴ ማን ናት ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አላቸው።

34. በዙሪያው ወደ ተቀመጡትም በመመልከት፣ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው!

35. የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴ፣ እናቴም ነውና።”