ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 26:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ይኸውም አንተ በተለይ የአይሁድን ልማድና ክርክር ሁሉ በሚገባ ስለምታውቅ ነው፤ ስለዚህ በትዕግሥት እንድታደምጠኝ እለምንሃለሁ።

4. “ገና ከልጅነቴ ጀምሮ፣ በአገሬም ሆነ በኢየሩሳሌም እንዴት እንደኖርሁ አይሁድ ሁሉ ያውቃሉ፤

5. ደግሞም ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለሚያውቁኝ ከሃይማኖታችን እጅግ ጥብቅ በሆነው ወገን ውስጥ ሆኜ እንደ አንድ ፈሪሳዊ መኖሬን ሊመሰክሩ ፈቃደኞች ከሆኑ ቃላቸውን ሊሰጡ ይችላሉ።

6. አሁንም ተከስሼ እዚህ የቀረብሁበት ምክንያት እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ቃል የገባውን ነገር ተስፋ በማድረጌ ነው።

7. ዐሥራ ሁለቱ ነገዶቻችን ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ከልብ እያገለገሉ፣ ሲፈጸም ለማየት የሚተጉለትም ተስፋ ይኸው ነው። ንጉሥ ሆይ፤ አይሁድም የሚከሱኝ ስለ ዚሁ ተስፋ ነው።

8. ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር ሙታንን ማስነሣት እንደማይችል አድርጋችሁ የምትጥቈሩት ለምንድን ነው?

9. “እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም በምችለው መንገድ ሁሉ መቃወም እንዳለብኝ ወስኜ ነበር።

10. በኢየሩሳሌምም ያደረግሁት ይህንኑ ነበር፤ ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብዬ ብዙ ቅዱሳንን አሳስሬ አለሁ፤ በመገደላቸውም ተስማምቻለሁ፤

11. ላስቀጣቸውም ብዙ ጊዜ ከምኵራብ ምኵራብ እየተዘዋወርሁ፣ የስድብ ቃል እንዲናገሩ አስገድዳቸው ነበር፤ በቍጣም ተሞልቼ በውጭ አገር እስከሚገኙ ከተሞች ድረስ ተከታትዬ አሳደድኋቸው።

12. “በዚህ መሠረት አንድ ቀን ከካህናት አለቆች ሥልጣንና ትእዛዝ ተቀብዬ ወደ ደማስቆ በምጓዝበት ጊዜ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 26