ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 21:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከእነርሱ ከተለየን በኋላ ቀጥታ በመርከብ ወደ ቆስ ተጓዝን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ አመራን።

2. በዚያም ወደ ፊንቄ የሚሄድ መርከብ ስላገኘን፣ ተሳፍረን ጒዞአችንን ቀጠልን።

3. ቆጵሮስ በታየችን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት ዐለፍንና ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከባችን ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለ ነበረበት፣ እኛም እዚያው ወረድን።

4. ደቀ መዛሙርትንም በዚያ አግኝተን፣ ሰባት ቀን ከእነርሱ ጋር ተቀመጥን። እነርሱም በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት።

5. የቈይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ፣ ትተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤

6. ከተሰነባበትንም በኋላ እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

7. ከጢሮስ ተነሥተን ጒዞአችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋር ቈየን።

8. በማግስቱ ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን።

9. እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።

10. በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤

11. ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ።

12. ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመነው።

13. ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳን ዝግጁ ነኝ” አላቸው።

14. ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።

15. ከዚህ በኋላ፣ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 21