ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐዋርያት ሥራ 2:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን?

8. ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድን በት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው?

9. እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጶዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣

10. በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብፅ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን

11. አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!”

12. ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ።

13. አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው።

14. በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንት የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ።

15. ጊዜው ገና ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም።

16. ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤

17. “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን፣መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ጒልማሶቻችሁ ራእይ ያያሉ፤ሽማግሌዎቻችሁ ሕልም ያልማሉ።

18. በዚያ ጊዜ በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ፣መንፈሴን አፈሳለሁ፤እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ።

19. በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ደምና እሳት፣ የጢስም ጭጋግ ይሆናል።

20. ታላቅና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።

21. የጌታን ስም፣የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐዋርያት ሥራ 2