ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 8:35-50 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

35. ሕዝቡም የተደረገውን ነገር ለማየት ከያሉበት ወጥተው ወደ ኢየሱስ መጡ። አጋንንት የወጡለትም ሰው ልብስ ለብሶ፣ ወደ ልቦናው ተመልሶ፣ በኢየሱስም እግር ሥር ተቀምጦ ባዩት ጊዜ ፈሩ።

36. በአጋንንት የተያዘው ሰው ሲድን ያዩትም፣ እንዴት እንደ ዳነ ለሕዝቡ አወሩላቸው።

37. የጌርጌሴኖን አካባቢ ሰዎችም ሁሉ ታላቅ ፍርሀት ስላደረባቸው፣ ከዚያ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ለመኑት፤ እርሱም ወደ ጀልባው ገብቶ ተመልሶ ሄደ።

38. አጋንንት የወጡለትም ሰው አብሮት ለመሆን ኢየሱስን ለመነው፤ እርሱ ግን እንዲህ ሲል አሰናበተው፤

39. “ወደ ቤትህ ተመልሰህ፣ እግዚአብሔር ያደረገልህን ታላቅ ነገር ተናገር።” ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ታላቅ ነገር በከተማው ሁሉ በይፋ እየተናገረ ሄደ።

40. ሕዝቡ ሁሉ መምጣቱን ይጠባበቁ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በተመለሰ ጊዜ በደስታ ተቀበሉት።

41. በዚህ ጊዜ ኢያኢሮስ የተባለ የምኵራብ አለቃ መጥቶ፣ በኢየሱስ እግር ላይ በመውደቅ ወደ ቤቱ እንዲሄድለት ለመነው፤

42. ይህን ልመና ያቀረበው ዕድሜዋ ዐሥራ ሁለት ዓመት የሆነ አንዲት ልጅ ስለ ነበረችው ነው፤ እርሷ በሞት አፋፍ ላይ ነበረች።ወደዚያው እያመራ ሳለ፣ ሕዝቡ በመጋፋት እጅግ ያጨናንቀው ነበር።

43. ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፤ ያላትን ሁሉ ለባለ መድኀኒቶች ጨርሳ ሊፈውሳትም የቻለ ማንም አልነበረም።

44. እርሷም ከበስተ ኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ይፈስ የነበረው ደሟም ወዲያው ቆመ።

45. ኢየሱስም፣ “የነካኝ ማነው?” አለ።ሁሉም መንካታቸውን በካዱ ጊዜ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ሕዝቡ ሁሉ ከቦህ በግፊያ እያስ ጨነቀህ ነው” አለው።

46. ኢየሱስ ግን፣ “አንድ ሰው ነክቶኛል፤ ኀይል ከእኔ እንደ ወጣ ዐውቃለሁና” አለ።

47. ሴትዮዋም ሳትታወቅ መሄድ እንዳልቻለች በተረዳች ጊዜ፣ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ ለምን እንደ ነካችውና እንዴት ወዲያው እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት ተናገረች።

48. እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ ፈውሶሻል፤ በሰላም ሂጂ” አላት።

49. ኢየሱስ ገና እየተናገረ ሳለ፣ አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ከኢያኢሮስ ቤት መጥቶ፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከዚህ በኋላ መምህሩን አታድክመው” አለው።

50. ኢየሱስም ይህን ሰምቶ ኢያኢሮስን፣ “አይዞህ አትፍራ፤ እመን ብቻ፤ ልጅህ ትድናለች” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 8