ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 7:32-47 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

32. በገበያ ቦታ ተቀምጠው እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ እንዲህ የሚባባሉ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም።’

33. ምክንያቱም መጥምቁ ዮሐንስ እህል ሳይ በላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፣ ጋኔን አለበት አላችሁት፤

34. የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፣ ‘በላተኛና ጠጪ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና “የኀጢአተኞች” ወዳጅ’ አላችሁት።

35. እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ ሁሉ ዘንድ ተረጋገጠ።”

36. ከዚህ በኋላ ከፈሪሳውያን አንዱ ምግብ አብሮት እንዲበላ ኢየሱስን ጋበዘው፤ እርሱም ወደ ፈሪሳዊው ቤት ሄዶ በማእድ ተቀመጠ።

37. በዚያ ከተማ የምትኖር አንዲት ኀጢአተኛ ሴት፣ ኢየሱስ በፈሪሳዊው ቤት በማእድ መቀመጡን በሰማች ጊዜ አንድ የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ሽቶ ይዛ መጣች፤

38. ከበስተ ኋላው እግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች እግሩን በእንባዋ ታርስ፣ በራሷም ጠጒር ታብሰው ጀመር፤ እግሩንም እየሳመች ሽቱውን ቀባችው።

39. የጋበዘውም ፈሪሳዊ ይህን ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው ነቢይ ቢሆን ኖሮ፣ የነካችው ሴት ማን እንደሆነች፣ ደግሞም ምን ዐይነት ሰው እንደሆነች ባወቀ ነበር፤ ኀጢአተኛ ናትና” ብሎ በልቡ አሰበ።

40. ኢየሱስም፣ “ስምዖን ሆይ፤ የምነግርህ ነገር አለኝ” አለው።እርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ንገረኝ” አለው።

41. ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “ከአንድ አበዳሪ ገንዘብ የተበደሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ አንደኛው አምስት መቶ ዲናር፣ ሁለተኛው ደግሞ አምሳ ዲናር ነበረበት።

42. የሚከፍሉትም ቢያጡ ዕዳቸውን ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከሁለቱ አበዳሪውን አብልጦ የሚወደው የትኛው ነው?”

43. ስምዖንም፣ “ብዙው ዕዳ የተተወለት ይመስለኛል” ሲል መለሰ።ኢየሱስም፣ “ትክክል ፈርደሃል” አለው።

44. ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ “ይህቺን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፤ አንተ ለእግሬ ውሃ እንኳ አላቀረብህልኝም፤ እርሷ ግን እግሬን በእንባዋ እያራሰች በጠጒሯ አበሰች።

45. አንተ ከቶ አልሳምኸኝም፤ እርሷ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም።

46. አንተ ራሴን ዘይት አልቀባህም፤ እርሷ ግን እግሬን ሽቶ ቀባች።

47. ስለዚህ እልሃለሁ፤ እጅግ ወዳለችና ብዙው ኀጢአቷ ተሰርዮላታል፤ በትንሹ የተሰረየለት ግን የሚወደው በትንሹ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 7