ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሉቃስ 5:12-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ኢየሱስ ከከተሞች በአንዱ በነበረበት ጊዜ፣ አንድ ለምጽ የወረሰው ሰው በዚያው ከተማ ነበር፤ ይህ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በፊቱ ተደፋና፣ “ጌታ ሆይ፤ ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው።

13. ኢየሱስም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና፣ “እፈቅዳለሁ፤ ንጻ!” አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ጠፋለት።

14. ኢየሱስም፣ “ይህን ለማንም አትናገር፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱ ምስክር እንዲሆንም ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን መሥዋዕት አቅርብ” ሲል አዘዘው።

15. ይሁን እንጂ ስለ እርሱ የሚወራው ወሬ ይበልጥ እየሰፋ ሄደ፤ እጅግ ብዙ ሰዎችም እርሱ የሚናገረውን ለመስማትና ካለባቸው ደዌ ለመፈወስ ይሰበሰቡ ነበር።

16. ኢየሱስ ግን ብዙ ጊዜ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ወጥቶ ይጸልይ ነበር።

17. አንድ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ነበር፤ በዚያም ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮች ሁሉ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር፤ ይፈውስም ዘንድ የጌታ ኀይል ከእርሱ ጋር ነበረ።

18. በዚያን ጊዜም፣ ሰዎች አንድ ሽባ በዐልጋ ተሸክመው አመጡ፤ ኢየሱስ ፊት ለማኖርም ወደ ቤት ሊያስገቡት ሞከሩ፤

19. ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ቤቱ ውስጥ ማስገባት ስላቃታቸው፣ ጣራው ላይ ወጥተው የቤቱን ክዳን በመንደል በሽተኛውን ከነዐልጋው በሕዝቡ መካካል ቀጥታ ኢየሱስ ፊት አወረዱት።

20. ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ፣ “አንተ ሰው፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።

21. ጸሐፍትና ፈሪሳውያንም፣ “ይህ አምላክን በመዳፈር እንዲህ የሚናገር ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ኀጢአትን ሊያስተስረይ ማን ይችላል?” ብለው ያስቡ ጀመር።

22. ኢየሱስም ሐሳባቸውን ስለ ተረዳ እንዲህ አላቸው፤ “ለምን በልባችሁ እንዲህ ታስባላችሁ?

23. ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል?

24. ነገር ግን ይህን ያልሁት የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ ነው።” ከዚያም ሽባውን ሰው፣ “ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሉቃስ 5